የመካነብርሃን-ዋሰል መንገድ ሥራ ፕሮጀክት የጠቅላላ ርዝመቱ 57%(ፐርሰንት) የሚሆነዉ የግንባታ ሥራ ተጠናቋል፤ በበጀት ዓመቱ የተለያዬ መጠን ያላቸዉ ስትራክቸሮች ግንባታም እየተከናወነ ነዉ፡፡

የአማራ ገጠር መንገዶች ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ በተያዘዉ በጀት ዓመት ለአነስተኛ፣መካከለኛ እና ትላልቅ ድልድዮች ግንባታ እንዲሁም ለቱቦ ቀበራ ሥራዎች ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ሲሆን በ2018 በጀት ዓመት የስትራክቸር ግንባታ ከሚከናወንባቸዉ ፕሮጀቶች መካከል በሰሜን ጎንደር ዞን ጃናሞራ ወረዳ የሚገኘዉ እና 52 ኪ.ሜ ርዝመት ያለዉ የመካነብርሃን-ዋሰል መንገድ ሥራ ፕሮጀክት አንዱ ነዉ፡፡

የመካነብርሃን -ዋሰል መንገድ ሥራ ፕሮጀክት በ2012 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን እስከ 2017 ዓ.ም ድረስ በተከናወነዉ ግንባታ የጠቅላላ ርዝመቱ 57.8% የሚሆነዉ የግንባታ ሥራ ተጠናቋል፡፡ፕሮጀክቱ በተያዘዉ በጀት ዓመት ከክልሉ መንግስት በተመደበ ከ23 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ በጀት ከ4 እስከ 15 ሜትር ርዝመት ያላቸዉ 3/ሦሥት/ አነስተኛ እና መካከለኛ ድልድዮች ግንባታ እንዲሁም የቱቦ ቀበራ ሥራዎችን ለማከናወን አቅዶ እየሰራ ሲሆን እስከ መጋቢት አጋማሽ 2018 ዓ.ም ድረስ በተከናወነዉ የግንባታ ሥራ የአንድ አነስተኛ ድልድይ ግንባታ ተጠናቋል፡፡ የ2 /ሁለት/ አነስተኛ እና መካከለኛ ድልድዮች ግንባታ ደግሞ የግንባታቸዉ 65% እና 20% ተከናዉኗል፡፡በ4/አራት/ ቦታዎች የሚከናወን የቱቦ ቀበራ ሥራም ተጠናቋል፡፡

የመካነብርሃን-ዋሰል መንገድ ሥራ ፕሮጀክት በክልሉ በሰሜን ጎንደር ዞን ጃናሞራ ወረዳ የሚገኙ እና በመንገድ ያልተገናኙ 7/ሰባት/ ቀበሌዎችን ርዕስ በርስ እና ከዋና መንገድ ጋር በማገናኘት የአካባቢዉን ህብረተሰብ የሚያጋጥሙ ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊ እና አስተዳደራዊ ችግሮች እንዲፈቱ በማድረግ ረገድ ጉልህ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡